ይህንን ድምፅ ከሰሙ በተለያየ መንገድ ወይም አጋጣሚ እዚህ ጣቢያ ደርሰዋል ማለት ነው። እንኳን ደህና መጡ። በዚህ የራዲዮ ጣቢያ ወይም ፖድካስት የሚተላለፉ መልዕክቶች ለሰሚው ማትረፊያ እንደሚሆኑ እምነታችን ነው።
የዚህ ፖድካስት አዘጋጅ እና አቅራቢ ኤፍሬም አይፎክሩ ሰለሞን እባላለሁ። የሪቪል መፅሔት ዋና አዘጋጅ ነበርኩ፤ እንዲሁም በተለያዩ የህትመት ሚዲያዎች ላይ በተለያየ የስራ ዘርፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳትፋለሁ። የመጀመሪያ ዲግሪዬን በኢኮኖሚክስ ሰርቻለሁ፤ በተጭማሪም በዚህ ወቅት ማስተርስ ዲግሪዬን እየተከታተልኩ እገኛለሁ። ሚስት አግብቻለሁ።
ይህንን ስርጭት ለመጀመር ያነሳሳኝ ዋነኛ ምክንያት ለራሴ እንደዚህ አይነት ዝግጅት ፈልጌ ማግኘት ስላልቻልኩ ሲሆን ሁሌም የመጀመሪያው አድማጭ እኔው እራሴው ነኝ ማለት ነው። ዝግጅቶቹ ለሁሉም ሰው ላይጠቅሙ ይችላሉ። ሊጠቅመው ለሚችል ሰው ግን እጅግ በጣም እንደሚጠቅመው አልጠራጠርም።
ዓለማችን በታሪኳ የቴክኖሎጂ ማማ ላይ የደረሰችበት እንደዚህ ያለ ዘመን ኖሮ አያውቅም። በተለይ የመረጃ ፍሰት መጠን አድጓል። መረጃን የሚሰበስቡ እና ማሰራጨት የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች በእያንዳንዱ ግለሰብ እጅ እየገባ ይገኛል። ሆኖም በዚህ ወቅት እየተፈጠሩ ባሉ ክስተቶች ላይ ግን መግባባት አልቻልንም። ብዙ መረጃ እና ማስረጃ ብዙ መግባባትና አንድነት ላይ አላደረሰንም።
ስለዚህ ያልመረጥነውን ብንሰማም የመረጥነውን ግን መቀበል እንችላለን። የመረጥነውን ማመን እንችላለን። ያመነው ታሪካችን ይሆናል። ምክንያቱም ታሪካችን የተቀበልነው ነው፤ ታሪካችን የምንገነባው ነው፤ ታሪካችን የምንተርከው ነው።
የኢትዮጵያን ታሪክ ኢትዮጵያውያን ይቀበሉት፤ ኢትዮጵያውያን ይምረጡት፤ ኢትዮጵያውያን ይገንቡት፤ ኢትዮጵያውያን ይተርኩት። ሰው ምንም እንኳ እውነት ብትነግረው የሚያምነው የፈለገውን ነው። ስለዚህ ሌላው ስለኛ ስለሚያምነው ሳይሆን እኛ ስለራሳችን የተቀበልነው ታሪክ ዋጋ አለው።
ስለዚህ በዚህ “ፖድካስት” እና ተያያዥ ስራዎቻችን የምናደርገው ይህንን ነው።
የዝግጅቱ አቀራረብ በ “ ሲዝን (S)" - ዋናው መነሻ ርዕስ ወይም ሃሳብ፥ “ ኤፕሶድ(E)" በዋናው ርዕስ ስር ያሉ ንዑስ ርዕሶች እና ሀሳቦች ሲሆኑ እና በዚያ “ ኤፕሶድ" ስር ያሉ ዝግጅቶች ደግሞ በ”ፓርት(P)” የተደራጁ ናችው።
ለምሳሌ የመጀመሪያው
- “ሲዝን (S01)” “ኢትዮጵያ፥ ኢትዮጵያዊ፥ ኢትዮጵያውያን መንደርደሪያ” የሚል ርዕስ ሲኖረው
- የመጀመሪያው “ኤፕሶድ(E01)” - "የዛሬዋ ኢትዮጵያ የጥንቷም ኢትዮጵያ ናት” የሚል ይሆናል።
- በዚህ ስር ያለው የመጀመሪያው ክፍል ወይም “ፓርት(P01)” ደግሞ - ኢትዮጵያ፥ ኢትዮጵያዊ፥ ኢትዮጵያውያን መንደርደሪያ የሚል ነው።
ማስታወሻ፦ በዚህ ቻናል ላይ የሚተላለፉ ዝግጅቶች በሌላኛው (IPedX Ethiopia) ቻናል ላይ በድጋሚ ተጭነው ሊገኙ ይችላሉ። ዝግጅቶቻችን በየትኛው የፖድካስት እና ሙዚቃ መስሚያ “አፕልኬሽን” ላይ ይገኛል።
Podchaser is the ultimate destination for podcast data, search, and discovery. Learn More